በየቦታው ግጭትና ሁከት በማስነሳት የዶ/ር አቢይን መንግስት ሀገሪቷን በሰላም ማስተዳደር አልቻለም የሚል እንድምታ

በየቦታው ግጭትና ሁከት በማስነሳት የዶ/ር አቢይን መንግስት ሀገሪቷን በሰላም ማስተዳደር አልቻለም የሚል እንድምታ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ
ሀይሎች እንዳሉ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። እነዚህ ላለፉት 27 አመታት ሀገሪቱን በብሄር ከፋፍለው ኢኮኖሚውን በአጥንቱ እስኪቀር ሲግጡ የነበሩ እና
በመከላከያውን፣ ደህንነቱን፣የፖሊስ ሀይሉን እና ሌሎችንም ግዙፍ የኢኮኖሚ ተቋማት እንደ ግል ርስታቸው ተቆጣጥረው የነበሩ ናቸው።
አሁን ህዝቡ አንቅሮ ስለተፋቸውና እንደ በፊቱ የመፍለጥ የመቁረጥ ስልጣናቸው እየተገዘገዘ በመዳከሙ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው
አህያ ሀገሪቱንና ህዝቡን ወደ ለየለት ብጥብት ለማስገባት በፌድራልና በክልል ባሏቸው ኔትወርኮች አማካኝነት እሳት የመጫር ሴራቸውን ጀምረዋል።
በአ.አ እና ሌሎችም ትላልቅ ከተሞች የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አልያም እንዲጠፋ በማረግ የኢኮኖሚ ሳቦታጅን ለህዝብ ብሶት እና
ተቃውሞ ማነሳሻ ለማድረግ ስራቸውን ጀምረዋል።
የትግራይ ህዝብንም ትኩረቱን ለማስቀየር በባድሜ ጉዳይ የረቀቀ ጨዋታቸውን አፋፍመዋል። ከመለስ ዜናዊ ጋር የባድሜን ጉዳይ ቁጭ ብለው
ተሰብስበው እንዲበላሽ እና የኢትዬጵያን ጥቅም አሳልፈው የሰጡት የህውሓት ሰዎች ዛሬ ደሞ ተገልብጠው ልክ በዶ/ር አቢይ እሚመራው መንግስት
የኢትዬጵያን መሬት እንደሰጠ አስመስለው እራሳቸውን ንፁህ ለማረግ እየሞከሩ ነው።
የኢትዬጵያ ህዝብ ከነ ልዩነቶቹ ለዘመናት ተቻችሎና ተዋልዶ በሰላም የኖረ ህዝብ ነው። በየትኛውም አለም ስልጣን ለመያዝና ግዛትን ለማስፋፋት ሲሉ
ገዢዎች በአንድ የተለየ ህዝብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱት ሁሉ የኢትዬጵያም አፄዎች ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀማቸው አይካድም። ይሁን እንጂ
በየትኛውም የኢትዬጵያ ታሪክ አንዱ ብሄር ጨቋኝ ሌላው ደሞ ተጨቋኝ ሆኖ አያውቅም። ኢህአዲግ ለከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ሲል አማራውን እንደ
ጨቋኝ አርጎ መርዝ ፕሮፖጋንዳውን ቢረጭም እንደ ብሄር አማራው ከሌላው የኢትዬጵያ ብሄሮች የጨቋኝነት ብቃት ሊያላብሰው የሚችል ቁመና ኖሮት
አያውቅም። የአማራው ገበሬ ከአቻ ኦሮሞው፣ትግሬው፣ሲዳማው ወይም ከሌላው ብሄር ምን የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ኖሮት ያውቃል? ከዚህ ብሄር
ወጥተው የገዢነት ስልጣን የነበራቸው አፄዎችና ተከታዬቻቸው በእርግጥ ተጠቃሚ ነበሩ። በአጭሩ ኢትዬጵያ ውስጥ የነበረው አሁንም ያለው ጭቆና
የተመሰረተው በመደብ ልዩነት እንጂ በብሄር ልዩነት አደለም።
ስለዚህ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የብሄር ግጭት እሚፈጥሩትን፣በየከተሞቹ ዝርፊያና ስርዕት አልበኝነት እንዲሰፍን እሚያረጉትን እና
የኢኮኖሚ ሳቦታጅ እሚፈፅሙትን ግለሰቦች/ሀይሎች ህዝቡ ሊያጋልጣቸውና ለፍርድ ሊያቀርባቸው ይገባል።
ገና በ3 ወር የጠ/ሚኒስቴርነት እድሜው ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን እያሳየ ያለውን ዶ/ር አቢይ ስልጣን ለማኮሰስ (undermine) ለማድረግ
በየአቅጣጫው እሚለኮሱ የግጭት እሳቶች ህዝቡ በማስተዋል ውሃ ሊቸልስባቸው ይገባል። ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው እነሱ
በሚቀሰቅሱት የብሄር ግጭቶች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተሳታፊ በመሆን የሀገራችንን ሀብት ቅርጥፍ አርጎው ሲበሉ ለቆዩት ሌቦችና ማፊያዎች
ተባባሪ ከመሆን እንቆጠብ።
እግዛብሔር ኢትዬጵያን ይባርክ!!!


Leave a Reply

Your email address will not be published.

Subscribe to Blog via Email

Enter your email address to subscribe to this blog and receive notifications of new posts by email.

Join 940 other subscribers